የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ህንጻ እና አስፓልት ግንባታ ፕሮጀክትን ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው፡፡

mazegaja1
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ህንጻ እና አስፓልት ግንባታ ፕሮጀክትን ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው፡፡

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት የአዲስ ህንጻ ግንባታ፣ ነባር ህንጻ እድሳት እና አስፓልት ግንባታ ፕሮጀክትን በኮንትራቱ ከተቀመጠለት ጊዜ ቀድሞ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የፕሮጀክቱ ኃላፊ አቶ ተስፋለም አድባሩ ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ 3000 ካሬ ሜትር የአስፓልት ንጣፍ፣ አዳዲስ ህንጻዎች ግንባታ፣ የነባር ህንጻ እድሳት፣ የመግቢያ በር ስራ እንዲሁም የግቢ ማስዋብ ስራዎች ግንባታን የሚያጠቃልል ሲሆን በጥሩ የግንባታ ፍጥነት ላይ እንደሆነ ባደረግነው ምልከታ ለመረዳት ችለናል፡፡

አስፓልት የማንጠፍ ስራው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን የነባር ህንጻ እድሳቱም ከፊኒሽንግ /የማጠናቀቂያ/ ስራዎች በስተቀር በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ የተለያዩ ቢሮዎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ካፍቴሪያና ሌሎች አዳዲስ ህንጻዎች ግንባታም ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ለግቢ ማስዋብ ስራው የሚያገለግል ከርቭ ስቶን የማምረት ስራ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን ሌሎች ስራዎችን ለመጀመርም ፕሮጀክቱ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡

እንደ ፕሮጀክት ኃላፊው ገለጻ ይህን ፕሮጀክት በ70 የስራ ቀናት ውስጥ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ውል የተያዘ ቢሆንም ከውል ጊዜው አስቀድሞ ለማጠናቀቅ ምሽትን ጨምሮ በሁለት ፈረቃ እየተሰራ ነው፡፡ እስካሁን ከሁለት ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ብቻ አጠቃላይ የፕሮጀክቱን ከ32 በመቶ በላይ ማከናወን እንደተቻለ የገለጹት ፕሮጀክት ኃላፊው ቀሪ ስራዎችንም እስከ ግንቦት 30 2016 ዓ.ም ለማጠናቀቅ አቅደው እየሰሩ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ ፕሮጀክቱ እስካሁን ባለው አፈጻጸም ደስተኛ እንደሆነና ቀሪ ስራዎችም በፍጥነት እንደሚጠናቀቁ እምነት እንዳለው እንዲሁም ድርጅታችን ከተለመደው የስራ ሰዓትና ባህል ባለፈ ተጨማሪ ሰዓት በመስራት አበረታች ውጤት በተግባር ማሳየት መቻሉ ትልቅ ትምህርት እንደሆናቸው ፕሮጀክት ኃላፊው አቶ ተስፋለም አድባሩ አስታውቀዋል፡፡

አማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ፕሮጀክቱን በፍጥነት ከማጠናቀቅ ባለፈ ከ11.9 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለውን 3000 ካሬ ሜትር አስፓልት ንጣፍ ስራ በነጻ ያከናወነ ሲሆን ለህዝብ የሚጠቅሙ መሰል የማህበራዊ አገልግሎት ተግባራትን የማከናወን ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ድርጅታችን ከዚህ በፊት በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የሚገኘውን የደብረ-ማርያም 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በራሱ ሙሉ ወጪ ገንብቶ ማስረከቡም የሚታወስ ነው፡፡


ድርጅታችን የሚያከናውናቸውን ተግባራት፣ የጨረታ እና የቅጥር ማስታወቂያዎችን ለማግኘት የድርጅታችንን፡-
ፌስ ቡክ፡ www.facebook.com/AmharaRoadWorksEnterprise
ድረ ገጽ፡ www.arwe.et
ቴሌግራም፡ www.t.me/AmharaRoadWorksEnterprise
ዩቲዩብ፡ www.youtube.com/AmharaRoadWorksEnterprise ይጎብኙ፡፡
mazagaja2