ያለፈውን በጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸም በያዝነው በጀት ዓመትም ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን የድርጅታችን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መብት አድማስ ገለጹ፡፡

bdr
ያለፈውን በጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸም በያዝነው በጀት ዓመትም ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን የድርጅታችን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መብት አድማስ ገለጹ፡፡

አማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት በአሁኑ ሰዓት ድርጅታችን ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ እና የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም በተመለከተ ለብዙሐን መገናኛ ተቋማት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የድርጅታችን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መብት አድማስ በ2015 በጀት ዓመት የተመዘገበውን የላቀ አፈጻጸም በ2016 በጀት ዓመትም ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ድርጅታችን በ2015 በጀት ዓመት አመራሮችና ሰራተኞች በደረሱበት የጋራ መግባትና የዓላማ ቁርጠኝነት በወቅቱ በኮንስትራክሽን ኢንደስትሪው የነበረውን ፈታኝ ሁኔታ በመቋቋም የላቀ አፈጻጸም ማስመዝገብ ችሏል፡፡ ድርጅታችን ውጤታማ ለማድረግ ሲባል ሰራተኛው በራሱ ተነሳሽነት ያለምንም ክፍያ በቀን ከ2-4 ተጨማሪ ሰዓት በመስራት ያለውን የባለቤትነት ስሜትና የሞራል ልዕልና ማሳየት የቻለበት ነው ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ በዚህም ድርጅቱ የነበሩ ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ባለፈው በጀት ዓመት ከትርፍ ግብር በፊት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገብ ችሏል በማለት ተናግረዋል፡፡ በተያያዘም ባለፈው በጀት ዓመት ከ320 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ ለመንገድ ስራው በእጅጉ አስፈላጊ የሆኑ 24 የተለያዩ ማሽነሪዎችን ግዥ መፈጸም ተችሏል፡፡ በተጨማሪም በዚህ በጀት ዓመት አንድ ዘመናዊ ክሬሸር ግዥ ተፈጽሟል፡፡

በያዝነው በጀት ዓመትም የነበረውን የላቀ አፈጻጸም ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ ይገኛል ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ ድርጅታችን በአሁኑ ሰዓት ካሉት ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ካላቸው 15 ፕሮጀክቶች መካከል በ2016 በጀት ዓመት የ5.8 ቢሊዮን ብር ስራ በመፈጸም 390 ሚሊዮን ብር ትርፍ ለማግኘት ዕቅድ በመያዝ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም በአማራ ክልል በባህር ዳር ከተማና በምስራቅ አማራ ያሉ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን እየተገነባ የሚገኘው የወራቤ ቦጆበር አስፓልት መንገድ ስራ ፕሮጀክት በጥሩ አፈጻጸም ደረጃ ላይ ይገኛሉ ብለዋል ዋና ስራ አስኪያጁ፡፡

በመጨረሻም ዋና ስራ አስኪያጁ እንደገለጹት ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል እየፈጠረ እና የማህበራዊ አገልግሎት ተግባራትን እያከናወነ የሚገኘው ድርጅታችን ይህንኑ መልካም ተግባር እንደሚያስቀጥል በመግለጽ ፕሮጀክቶች በሚገነቡባቸው አካባቢዎች የሚገኘው ህብረተሰብ የተቋሙን እና የህዝብን ንብረት ከጉዳት እንዲከላከልና ለፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት መጠናቀቅ የበኩሉን ጥረት እዲያደርግ አሳስበዋል፡፡

ድርጅታችን የሚያከናውናቸውን ተግባራት፣ የጨረታ እና የቅጥር ማስታወቂያዎችን ለመከታተል፡-
ፌስ ቡክ፡ www.facebook.com/AmharaRoadWorksEnterprise
ድረ ገጽ፡ www.arwe.et
ቴሌግራም፡ www.t.me/AmharaRoadWorksEnterprise
ዩቲዩብ፡ www.youtube.com/AmharaRoadWorksEnterprise ይጎብኙ፡፡
bdr