የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ከባህር ዳር ከተማ አስተዳደር አመራሮች ጋር በዳንግላ ከተማ ውይይት አደረገ

የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ከባህር ዳር ከተማ አስተዳደር አመራሮች ጋር በዳንግላ ከተማ ውይይት አደረገ
የውይይት ኘሮግራሙ የጀመረው የዳንግላ ጃዊ የጠጠር መንገድ ሥራ ኘሮጀክትን በመጎብኘት ነበር፡፡ የውይይቱ ተሣታፊዎች የጉብኝት ኘሮግራሙን አጠናቀው እንደተመለሱ የኘላንና ቢዝነስ ደቨሎኘመንት ደጋፊ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አያልነህ ገሰሰ የድርጅቱን የ6 ዓመት የእድገት ጉዞን አቅርበዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የተገኙት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙሉቀን አየሁ የዳንግላ ጃዊ የጠጠር መንገድ ጉብኝት እና የድርጅቱን የዕድገት ጉዞ መነሻ በማድረግ ድርጅቱ በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአስቸጋሪ የመሬት አቀማመጥ ውስጥ ገብቶ 75 ሜትር ከፍታ ያለውን ጠንካራ አለት ከሁለት ሰንጥቆ የመንገድ መልክ ማስያዝ የቻለ መሆኑን ስንመለከት ከፍተኛ ኩራት ተሰምቶናል ያሉ ሲሆን ድርጅቱንም ለአንድ ጊዜ የኛ መንገድ ሥራዎች ድርጅት በማለት በአንድ ድምፅ በከንቲባው መሪነት እንዲጠራ አድርገዋል፡፡

ከንቲባው አያይዘውም በቀጣይ ድርጅቱ ከዚህ በበለጠ ተጠናክሮ ተወዳዳሪና ተመራጭ ሆኖ እንዲቀጥል የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ከጎናችሁ እንሰለፋለንም ብለዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት የከተማ አስተዳደር አመራሮች እና የክፍለ ከተማ አመራሮችም በበኩላቸው በክልላችን በአስፓልት እና በጠጠር የመንገድ ግንባታ ዘርፍ አቅም ያለው ጠንካራ ድርጅት መኖሩን በማወቃችን ትልቅ ኩራት ተሠምቶናል ካሉ በኋላ አመራሮቹ የመንገድ ሥራ ድርጅትን በዚህ ልክ ይገምቱት እንዳልነበር ገልፀው ድርጅቱ ተጠናክሮ ራዕዩን ማሣካት እንዲችል የከተማ አስተዳደሩ ከድርጅቱ ጋር በጋራ መሥራት እንዳለበት ሀሣባቸውን ሠጥተዋል፡፡
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አመራሮች በመድረኩ አማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅትን ሲገልጹ መንገድን በጥራት የመገንባት አቅምን ያየንበትና የተረዳንበት ከመሆኑም በላይ በቀጣይ አብሮ ለመስራት ዕድልን ፈጥሮልናል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ አስማማው ዓለማየሁ ጥሪያችንን አክብረው በውይይት መድረኩ ለተገኙ የከተማ አስተዳደር እና ክፍለ ከተማ አመራሮችን አመስግነው መድረኩ ተጠናቋል፡፡