የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት የ2016 በጀት ዓመት የ9 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ተካሄደ፡፡

1
የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት የ2016 በጀት ዓመት የ9 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ተካሄደ፡፡

የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት የ2016 በጀት ዓመት የ9 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ የድርጅታችን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መብት አድማስን ጨምሮ የማኔጅመንት አባላት እና ሁሉም የዋና ቢሮ ሰራተኞች በተገኙበት ዛሬ ሚያዚያ 21/2016 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡ የበጀት ዓመቱ የ9 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በፕላንና ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ደጋፊ ስራ ሂደት መሪ አቶ ተገኘ ወርቁ ቀርቦ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ውይይቱን የድርጅታችን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መብት አድማስ እና የኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ገበያው መንግስቴ መርተውታል፡፡
በዕቅድ አፈጻጸም ግምገማው የተሳተፉት የድርጅታችን ሰራተኞች በቀረበው ሪፖርት ላይ የተለያዩ አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን በማንሳት በሰፊው የተወያዩ ሲሆን በተለይ አጠቃላይ የኮንስትራክሽን ኢንደስትሪው በተፈተነበትና በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታው ምክንያት ዋና ዋና ፕሮጀክቶቻችን ስራ ባቆሙበት በጀት ዓመት በሌሎች ፕሮጀክቶች አመራሩና ሰራተኛው ርብርብ በማድረግ ድርጅታችን ትርፍ እንዲያስመዘግብ ማድረግ በመቻሉ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ወቅታዊ ሁኔታው የደቀነው ችግር ድርጅታችንን በከፍተኛ ሁኔታ እንዳይጎዳው በበጀት ዓመቱ የድርጅታችን አመራሮች የተከተሉት ብስለት የተሞላበት የአመራር ጥበብ እና ቁርጠኝነት የተሞላበት የውሳኔ አሰጣጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው ሲሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በተሳታፊዎች ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች በመድረኩ አወያዮች ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ድርጅታችን በበጀት ዓመቱ 9 ወራት ያስመዘገበው የዕቅድ አፈጻጸም ከነበሩት ፈታኝ ሁኔታዎች አንጻር ሲታይ ትልቅ ውጤት ነው ያሉት አወያዮቹ በተለይ ለስራ ምቹ ባልሆኑ ሁኔታዎች እና አካባቢዎች ጭምር ከመደበኛው የስራ ሰዓት ውጪ ተጨማሪ ሰዓት በመስራት ለድርጅታቸው ከፍተኛ የባለቤትነት ስሜት እያሳዩ የሚገኙ ሰራተኞችን ማመስገንና እውቅና መስጠት ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በተያያዘም በቀሪ የስራ ወራት በሙሉ አቅም አሟጦ በመስራት ከእስካሁኑ የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ የጋራ ርብርብ ሊደረግ እንደሚገባም በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡ ሰራተኛውም ሊጠቀም የሚችለው ድርጅቱ አትራፊ ሲሆን በመሆኑ ሁሉም አመራርና ሰራተኛ ድርጅቱን በየኔነት ስሜት ማገልገል እንዳለበትና በተቻለ መጠን ሰራተኛው ተጠቃሚ የሚሆንበትን ስራ እንደሚሰሩ አመራሮቹ አረጋግጠዋል፡፡

በመጨረሻም በቀጣይ ሁለት ወራት በየደረጃው የሚገኙ አመራርና ሰራተኞች በዘጠኝ ወራት ያሳያችሁት የመፈጸም ብቃት፣ ትጋት እና የባለቤትነት ስሜት በእጅጉ የሚመሰገን እና የሚደነቅ ከመሆኑም በላይ አጠናክሮ በማስቀጠል ድርጅታችን በማይቀለበስ መሰረት ላይ ማስቀመጥ ይገባናል በማለት ውይይቱ ተጠናቋል፡፡
2