የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት አመራሮች እና ሰራተኞች በህልውና ማስከበር ዘመቻው ለተሰማራው ጀግናው ሰራዊታችን የሚያደርጉትን የስንቅ ዝግጅት አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡


ኢትዮጵያን ማፍረስ በተለይም አማራን ማጥፋት ካልቻለም ማዳከም ዋና ዓላማ አድርጎ እየተውተረተረ የሚገኘው ትህነግ በአማራ እና አፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች ሰላም የመንሳትና የማሸበር እኩይ ድርጊት እየፈጸመ ይገኛል፡፡ ትህነግ ለሶስት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያን ሲዘርፋትና በአለም አደባባይም አንገቷን ሲያስደፋት ቆይቶ በመላ ኢትዮጵያውያን ትግል ከማዕከላዊ መንግስት ቢገለልም እኔ ያልመራኋት ሀገር ትፍረስ በሚል ሰይጣናዊ እሳቤው የኢትዮጵያውያንን ልማትና እድገት ከማይፈልጉና በባንዳነት ከሚያገለግላቸው የውጭ ሀይሎች እንዲሁም እሱን አስመስሎ በሰራቸው ውስጣዊ ጸረ ሰላም ሀይሎች በመታገዝ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየደከመ ነው፡፡ አሁንም ጥላቻንና እርስ በርስ መጠፋፋትን የሚሰብከው ትህነግ በደረሰባቸው አካባቢዎች ሁሉ ህጻናትን ጨምሮ ንጹሀንና ሰላማዊ ዜጎችን በግፍ መግደል እንዲሁም ሀብትና ንብረትን መዝረፍ የዘወትር ተግባሩ አድርጎታል፡፡

ይህን አሸባሪ ቡድን የሰነዘረውን ጥቃት ለመመከትና ቡድኑ የደህንነት ስጋት የማይሆንበት ደረጃ ላይ ለማድረስ የክልላችንና የፌዴራል መንግስት የተቀናጀ የህልውና ማስከበር ዘመቻ ከፍተዋል፡፡ በተለያዩ ግምባሮች የተሰማራው ጀግናው ሰራዊታችን በእብሪተኛው ቡድን ላይ በአጭር ጊዜ ድል እንደሚቀዳጅም አያጠራጥርም፡፡ የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት አመራሮች እና ሰራተኞችም ጦር ግምባር ለተሰማራው ጀግናው ሰራዊታችን የሚያደርጉትን የስንቅ ዝግጅት አጠናክረው በመቀጠል ደጀንነታቸውን እያስመሰከሩ ነው፡፡ ለሰራዊታችን በድምሩ 45 ኩንታል በሶ አዘጋጅቶ ለመላክ የታቀደ ሲሆን የመጀመሪያውን ዙር 15 ኩንታል ያጠናቀቀ ሲሆን በቅርቡ ይላካል፡፡ በተጨማሪም የድርጅታችን አመራሮች እና ሰራተኞች ሙሉ የወር ደመወዛቸውን ለህልውና ማስከበር ዘመቻ መስጠታቸው የሚታወስ ሲሆን በቀጣይ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡