በድርጅታችን እየተገነባ የሚገኘው ነባሩ የባህር ዳር ከተማ መነሀሪያ አስፓልት ኮንክሪት ግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑን በፕሮጀክቱ ባደረግነው ምልከታ ለመረዳት ችለናል፡፡ በድርጅታችን በባህር ዳር ከተማ እየተገነቡ ከሚገኙት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የባህር ዳር ከተማ ነባሩ መነሀሪያ አንዱ ሲሆን ግንባታው የተጎዳውን ነባሩን አስፓልት አንስቶ ደረጃውን በማሳደግ እና ጥራቱን በመጠበቅ የሚገነባ አስፓልት ኮንክሪት የማልበስ ስራ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ በኪሎ ሜትር ሲገለጽ 1.81 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 7 ሜትር ስፋት እንዲሁም 10 ሳ.ሜ ውፍረት ያለው ባለ-ሁለት ሌየር አስፓልት፣ የእግረኛ መንገድ እና የማፋሰሻ ስራዎችንም ያካትታል፡፡
በአሁኑ ሰዓት የግንባታ ፕሮጀክቱ የጠንካራ አለት ሙሊት፣ ሰብ ቤዝ፣ ቤዝኮርስና የማፋሰሻ ስራዎች ተጠናቀው አስፓልት እየለበሰ ሲሆን አስፓልት የማልበስ ስራው 80 ከመቶ ደርሷል፡፡ 90 ሜትር ደብል ፓይፕ እና 130 ሜትር የማሶነሪ ማፋሰሻ ስራዎችም ሙሉ በሙሉ ተጠናቀዋል፡፡ የእግረኛ መንገድ ግንባታውም የሙሊት ስራው የተጠናቀቀ ሲሆን ባዞላ የማንጠፍ ስራውን በቅርቡ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው፡፡ በአጠቃላይ ፕሮጀክቱን በፍጥነት ለማጠናቀቅና ሙሉ በሙሉ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ በፕሮጀክቱ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡