የላሊበላ አሹዳ ዝህብስት ፈንድቃ መንገድ ስራ ፕሮጀክት አፈፃፀም 98 ከመቶ በላይ መድረሱ ተገለፀ።


የምዕራብ ጎጃሟን ደቡብ አቸፈር ወረዳ ከአዊ ዞን ጃዊ ወረዳ ጋር የሚያገናኘው የላሊበላ አሹዳ ዝህብስት ፈንድቃ መንገድ ስራ ፕሮጀክት 98 ከመቶ በላይ መጠናቀቁ ተገለፀ። ይህ መንገድ ስራ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 67 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 7 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን ትልልቅ ድልድዮች፣ ስትራክቸር፣ ቱቦ ከልቨርት፣ ስላቭ ከልቨርት እና ሌሎች ስራዎችን የያዘ ነው። መንገዱ በተለይ 60 ሜትር ርዝመት ያለውን ግዙፉን የበለስ ወንዝ ድልድይ እንዲሁም 22 ሜትር ርዝመት ያለውን የጋንክ ወንዝ ድልድይ ጨምሮ ሌሎች አስቸጋሪና እስከ 39 ሜትር ከፍታ የሚደርስ የአለት ቆረጣ የጠየቀ ነው። ይሁን እንጅ ለአስቸጋሪ መልክዓ ምድር የማይበገረው አማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት የመንገዱን ግንባታ አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ የሚቀረው በበለስ ወንዝ ላይ የሚገነባው ድልድይ ነው።

ድርጅታችን መንገዱን በፍጥነት አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ ፕሮጀክቱን በሁለት ሎት ከፍሎ ነው እየገነባ የሚገኘው። ሎት አንድ ከላሊበላ አሹዳ ዝህብስት በለስ ወንዝ ያለውን 52 ኪ.ሜ መንገድ የሚሸፍን ሲሆን እስከ 39 ሜትር የሚደርስ የአለት ቆረጣ የሚገኝበት ክፍል ነው። በዚህ ሎት የመንገድ ጠረጋ፣ የስትራክቸርና ውሀ ማፋሰሻ ስራዎች ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቁ ሲሆን የሚቀረው የማስተካከያ ስራና 60 ሜትር ርዝመት ያለው የበለስ ወንዝ ድልድይ ብቻ መሆኑን የፕሮጀክቱ ተወካይ ሀላፊ አቶ መሳይ ሰጥአርጌ ተናግረዋል። እንደ ተወካይ ፕሮጀክት ሃላፊው ገለፃ የበለስ ወንዝ ድልድይ 60 ሜትር ርዝመት እና 8.92 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ ቢታቀድም የዲዛይን ችግር በወቅቱ ባለመፈታቱ እና የግብዓት አቅርቦት ውስንነት በመኖሩ ማጠናቀቅ ባይቻልም የድልድይ ግንባታ ስራው በመጠናቀቅ ላይ በመሆኑ የሚቀረው የፒርና ስላቭ ስራ ብቻ በመሆኑ እስከ 2013 ዓ.ም አጋማሽ ባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ ታቅዷል ።

ሎት ሁለት ደግሞ ከፈንድቃ (ጃዊ) ከተማ እስከ በለስ ወንዝ ያለውን 15 ኪ.ሜ መንገድ የሚሸፍን ሲሆን አካባቢው ረግረጋማና ጥቁር አፈር በመሆኑ ጥቁር አፈሩን ቆርጦ የማስወገድና በሌላ አፈር የመሙላት ስራ እንዲሁም የጋንክ ወንዝ ድልድይን ጨምሮ የስትራክቸርና 35 የቱቦ ከልቨርት ስራዎች ተጠናቀዋል። የፕሮጀክቱ ተወካይ ሀላፊ አቶ ያስችላል አሻግሬ እንደገለፁት መንገዱ በኪሎ ሜትር ደረጃ ትንሽ ቢሆንም የጋንክ ወንዝ ድልድይ እና የስትራክቸር ስራዎች መብዛታቸው መንገድ ስራውን ፈታኝ አድርጎት ነበር። በተለይ የጋንክ ወንዝ ድልድይን የብረት ኢንስታሌሽን ስራ አጠናቀው አርማታ ለመሙላት ሲዘጋጁ ከጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክት ግድብ የተለቀቀ ውሃ ለሁለት ጊዜ ሙሉ በሙሉ እንደወሰደባቸውና ለሶስተኛ ጊዜ የውሃውን አቅጣጫ ቀይረው በማፋሰስ ለመስራት መገደዳቸው የስራውን አስቸጋሪነት ከማሳየቱም በላይ ረጅም ጊዜ እንደወሰደባቸው ተወካይ ፕሮጀክት ሃላፊው አቶ ያስችላል ገልፀዋል።