ለአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት የዋና ቢሮ እና የፕሮጀክቶች ማኔጅመንት አባላት የ2012 እቅድ አፈጻጸምን መነሻ ያደረገ ግምገማ አዘል ስልጠና ተሰጠ ።


የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ለዋና ቢሮ እና ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት አባላት የ2012 እቅድ አፈጻጸምን መነሻ ያደረገ ግምገማ አዘል ስልጠና ከመስከረም 19 እስከ 23 2013 ዓ.ም ሰጥቷል።
ግምገማው በድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አስማማው አለማየሁ የተመራ ሲሆን በሎጅስቲክስ ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ሞላ ባይሌ እና በኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ግርማው እንዲሁም በዋናው ቢሮ የማኔጅመንት አባላት ለፕሮጀክቶች አፈጻጸም ችግር ሆነው የታዩትን የአመለካከት፣ የአሰራር፣ የአደረጃጀት እና የግብዓት አቅርቦት እና አጠቃቀም ጉድለቶች እንዲሁም የካይዘን ፍልስፍናን የስራ ማሳለጫ አድርጎ በመጠቀም በኩል የታዩ ጉድለቶች የሚያመላክቱ የውይይት መነሻ ሃሳቦች ቀርበዋል፡፡
የቀረቡትን የመነሻ ሀሳቦች መሰረት በማድረግ በንብረት አያያዝ እና አስተዳደር፣ በመሳሪያዎች አስተዳደርና ጥገና፣ በቴክኖሎጅ አጠቃቀም፣ በዕቅድ ዝግጅት ክትትልና ሪፖርት፣ በፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ በኮንትራት አስተዳደር፣ በካይዘን ትግበራ እና የውስጥ ኦዲት የምርመራ ሂደት በተገኙ የአሰራር ክፍተቶች ዙሪያ በ2012 በጀት ዓመት በጥንካሬና በጉድለት የተስተዋሉ ጉዳዮች ተነስተው ውይይትና ግምገማ ተካሂዶባቸዋል።
ድርጅቱ ለሰራቸው ስራዎች ክፍያ በወቅቱ ማግኘት ባለመቻሉ በተፈጠረ የካሽ እጥረት ምክንያት የተከሰተው የግብዓት አቅርቦት ችግር በበጀት ዓመቱ የድርጅቱ ዕቅድ አፈፃፀም ላይ ጉልህ ተፅዕኖ እንደነበረው በመድረኩ ተነስቷል። በተጨማሪም ጥንካሬዎች እንደተጠበቁ ሁነው የጊዜ፣ የማሽነሪ፣ የሰው ሀይል ብክነት፣ ግዥን በዕቅድ ያለመምራት ችግር፣ ሥራን በጠራ፣ ጤናማ በሆነ አመለካከት እና የአሰራር ስርዓትን ተከትሎ ያለመምራት ችግር፣ የካይዘን ስራ አመራር ፍልስፍናን የስራ ማሳለጫ አድርጎ በመጠቀም እና ብክነትን ለመከላከል የሚደረገው የስነ ልቦና ዝግጅት በሚፈለገው መጠን ሆኖ አለመገኘት፣ በውስጥ ኦዲት የሚደረጉ የምርመራ ግኝቶችን በአስተማሪነቱ ወስዶ ለማስተካከል የሚደረግ ጥረት በሚፈለገው ልክ ሆኖ አለመገኘት በመድረኩ በሰፊው ከተነሱት ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

እንደ አትራፊ ድርጅት ፕሮጀክት የማስተዳደር አቅምን ማጎልበት፣ የብክነት መንስኤዎችን መለየትና ችግሩን ለመቅረፍ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት መተግበር፣ ቴክኖሎጅን መጠቀም እንዲሁም ከንብረት ክፍል ወጭ የተደረጉ ንብረቶች በአግባቡ ስራ ላይ መዋላቸውን መከታተልና ችግሮች ሲፈጠሩም የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑ በከፍተኛ ደረጃ ተገልጿል።
በድርጅቱ የሚስተዋሉ የአመለካከት ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲቻል በርካታ ስልጠናዎችን በተለያዩ ጊዜያት ለሁሉም የድርጅቱ አመራሮች እና ባለሙያዎች እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ በሌላ በኩል ስራዎችን ወጥነት ባለው የአሰራር ስርዓት ለመፈጸም እና ለማስፈጸም በአዲስ መልክ የአሰራር ስርዓት ተዘጋጅቶ እስከ ፕሮጀክቶች መውረዱን በመጥቀስ በስልጠናዎች የተገኙ ግብዓቶችንም ሆነ የአሰራር ስርዓቱን በትክክል ተግባር ላይ ማዋል እንደሚገባ ተገልጿል።
በመጨረሻም የ2012 በጀት ዓመት የታዩ ጠንካራ ጎኖች እንደተጠበቁ ሆነው ለእቅድ አፈጸጸም ችግር ሆኖ የተነሳውን የአመለካከት ችግሮች እና ይህንን ተከተሎ የሚፈጠረውን የአሰራር፣ የግብዓት አቅርቦት እና አጠቃም እና መሰል ችግሮች ሲፈጠሩ ከዋና ቢሮ እስከ ፕሮጀክት ድረስ የድርጅቱን የአሰራር መመሪያን በጠበቀ መንገድ አስተማሪ የሆነ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ታውቆ በየደረጃው የሚገኝ የስራ መሪ በንቃት፣ በትጋት እና በታማኝነት ስራዎችን መፈጸም እና ማስፈጸም እንዳለባቸው የመድረኩ የጋራ ሃሳብ ሆኖ ግምገማው ተጠናቋል፡፡