አማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሻለ ለውጥ ማስመዝገብ የቻለ የክልላችን ተቋም ነው ሲሉ የአብክመ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ድጋፍና ክትትል ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መጋቢያው ጣሰው ተናገሩ።

መ

አማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት በተመሰረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣን እድገትና የተሻለ ለውጥ ማስመዝገብ የቻለ የክልላችን ተቋም ነው ሲሉ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ድጋፍና ክትትል ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መጋቢያው ጣሰው ተናገሩ። የክልሉን የመሰረተ ልማት ተደራሽነት እና ሁለንተናዊ ለውጥ ለማረጋገጥ አስፈላጊነታቸው ታምኖበት ከተቋቋሙት የመንግስት የልማት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው አማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት በአሁኑ ሰዓት ትልልቅ የአስፓልት እና ጠጠር መንገድ ሥራ ፕሮጀክቶችን ይዞ በመገንባት ላይ ይገኛል።

ድርጅቱ በሚገነባቸው ጥራት ያላቸው መንገዶች ከክልል አልፎ በፌዴራል ደረጃ እውቅና አግኝቶ በክልሉና ከክልሉ ውጭ ትልልቅ የአስፓልት መንገድ ስራ ፕሮጀክቶችን እየገነባ መሆኑ እና በተለይ ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ያስመዘገበው የተሻለ አፈፃፀም ድርጅቱ በጥሩ የእድገት ደረጃ ላይ መገኘቱ እንዲሁም በካይዘን ስራ አመራር ፍልስፍና ትግበራ የተሻለ አፈፃፀም በማሳየት ከክልላችን አልፎ በሀገር ደረጃ ካይዘንን እየተገበሩ ከሚገኙ ተቋማት ጋር ተወዳድሮ አንደኛ ደረጃን ማግኘቱም ተቋሙ በእድገት ጉዞ ላይ የመሆኑ ሌላው ማሳያ እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። ድርጅቱ ከተመሰረተ አጭር ጊዜ በመሆኑ እና ወደ አስፓልት ስራ የገባው በቅርቡ ቢሆንም በገነባቸው የአስፓልት መንገድ ስራ ፕሮጀክቶች ምንም አይነት የጥራት ጉድለት ያልታየ መሆኑ ድርጅቱ መንገዶችን በጥራት የመገንባት ብቃት እንዳለው ያሳያል ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ድርጅቱ በብዙ መሰናክሎች ውስጥ ሆኖ የተሻለ አፈፃፀም ማሳየቱ የሚደነቅ ቢሆንም ካለበት የእድገት ጉዞ ወደ ኋላ እንዳይመለስ በአፈፃፀሙ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ችግሮችን በመፍታት ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል ብለዋል። በመጨረሻም አማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት የሚፈለገው ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ የድጋፍና ክትትል ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።