አማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት አለት ሰንጥቆ ጥራት ያለው መንገድ የመገንባት አቅም ያለው ድርጅት ነው ሲሉ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ደሳለኝ ወዳጀ ተናገሩ። የዳንግላ ጃዊ፣ ላሊበላ አሹዳ ዝህብስት ፈንድቃና አርብ ገበያ ጋግቢያ ኩርባ መንገድ ስራ ፕሮጀክቶች የድርጅቱን አቅም ማሳያ ፕሮጀክቶች ናቸው ያሉት አቶ ደሳለኝ በተለይም አስቸጋሪ የመሬት አቀማመጥና ከፍተኛ የሆነ አለት ባለው የዳንግላ ጃዊ መንገድ ስራ ፕሮጀክት አለት ሰንጥቆ መንገድ በመስራት ድርጅቱ አቅም እንዳለው አስመስክሯል ሲሉ ገልፀዋል።
የዳንግላ ጃዊ መንገድ ስራ ፕሮጀክት 70 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 7 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን ከፍተኛ የሆነ የጋራና አለት ቆረጣ ስራ ያለበት አስቸጋሪ የመንገድ ስራ ፕሮጀክት ነው። በተለይም ከጠቅላላ መንገድ ስራው 7.6 ኪሎ ሜትር የሚሆነው የመንገዱ ክፍል እስከ 70 ሜትር የሚደርስ የጠንካራ አለት (hard rock) ቆረጣና የፍንዳታ ስራ የጠየቀ ነበር። በአብዛኛው እንደዚህ አይነት የመንገድ ስራ ፕሮጀክቶች የሚገነቡት በውጭ ሀገር ኮንትራክተሮች የነበረ ቢሆንም አማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ግን ይህን አስቸጋሪ መንገድ በጥራት በመገንባት አቅሙን አሳይቶበታል።
የዳንግላ ጃዊ ጠጠር መንገድ ስራ ፕሮጀክት ሁለቱን የአማራ ክልል ወረዳዎች ማለትም ዳንግላ እና ጃዊን እንዲሁም ከሁለቱ ወረዳዎች ባለፈ የአማራ ክልልን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው መንገድ ነው። ይህን ባለ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ የመንገድ ስራ ፕሮጀክት ለመገንባት ከአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ጋር ኮንትራት የተፈራረመው አማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት መንገዱን በጥራት ገንብቶ በማጠናቀቁ በአሁኑ ሰዓት መንገዱ ክረምት ከበጋ ለተሽከርካሪ ክፍት ሆኖ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
ከዳንግላ ወርቅ ሜዳ እና ከባህር ዳር ጃዊ የጭነት አገልግሎት በመስጠት ስራ ላይ የተሰማሩ አሽከርካሪዎችም በበኩላቸው በየቀኑ በዘህ መስመር እንደሚመላለሱ ገልፀው ይህ መንገድ ከመሰራቱ በፊት በተራራው ጭነው መውጣት ስለማይችሉ በግልገል በለስ ዙረው ረጅም ርቀት ለመጓዝ ይገደዱ እንደነበርና የዚህ መንገድ መሰራት እንግልታቸውን እንደቀነሰላቸው ተናግረዋል።