የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የውስጥ ለውስጥ አስፓልት መንገድ ጥራቱን ጠብቆ መገንባቱ ተገለፀ።


በአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት የተገነባው የኢንዱስትሪ ፓርኩ የውስጥ ለውስጥ አስፓልት መንገድ በአይነቱ የተለየ እጅግ ውስብስብ እና ከዚህ ቀደም በሀገር ደረጃ እንኳን ያልተለመዱ አዳዲስ ቴክኖሎጅዎች የተተገበሩበት እንደነበር የመንገድ ስራ ፕሮጀክቱ ተወካይ ሀላፊ አቶ በላንተ ፀጋየ ይናገራሉ። ከተተገበሩ አዳዲስ ቴክኖሎጅዎች መካከል የመንገዱን ጥንካሬ ለመጨመር አፈርን በኖራ የማከም ስራ (lime stabilization) አንዱ ነው። ይህ መንገድ ከባድ ጭነት የጫኑ ተሽከርካሪዎች በሚጓዙበት ወቅት ጉዳት እንዳይደርስበት በአስፓልት የተገነቡ ሶስት ደረጃዎች ያሉት ቤዝ ኮርስ እና አስፓልቱን ጨምሮ ደግሞ በጥቅሉ 31 ሳ.ሜ ውፍረት ያለው ደረጃውን ጠብቆ የተገነባ አስፓልት መንገድ ነው።

ከ10 እስከ 30 ሜትር የሚደርስ ስፋት እና 11.2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኢንዱስትሪ ፓርኩ የውስጥ ውስጥ አስፓልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ያለ ሲሆን አፈፃፀሙ ከ 95 % በላይ ደርሷል። የተረፈ ምርት/ቅሪት ማስወገጃ፣ የውሃ ማፋሰሻ፣ የኔትወርክ መስመር ግንባታ ስራዎች በጥራት ተገንብተው የተጠናቀቁ ሲሆን የLow Voltage እና Midium Voltage ኤሌክትሪካል ስራው ደግሞ ቪስታ ኮንስትራክሽን ኃ.የተ.የግል ማህበር እና ሩት ኤሌክትሮ መካኒካል ኢንጅነሪንግ ለተሰኙ ድርጅቶች በሰብ ኮንትራት ውል ወስደው እየሰሩ ይገኛሉ።

የመንገዱ የጥራት ሁኔታ እንዴት ይገመገማል ስንል የጠየቅናቸው የመንገድ ስራ ፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ መሀንዲስ አቶ አብዩ ጥላሁን የአስፓልት መንገድ ስራ ፕሮጀክቱ ጥራቱን ጠብቆ መገንባቱን ገልፀዋል። አቶ አብዩ እንዳሉት በፕሮጀክቱ የተመደቡ ባለሙያዎች የተሻለ ልምድ እና እውቀት ያላቸው በመሆናቸው እንዲሁም እያንዳንዱ ስራ ሲሰራ በአማካሪ በኩል ቴስት እየተሰራና ጥብቅ የሆነ ቁጥጥር እየተደረገ በመሆኑ ምንም አይነት የጥራት መጓደል ችግር አልተከሰተም።