ስለ ድርጅቱ

ከየት ወዴትራዕይ ተልዕኮ ዋና እሴቶች   | አገልግሎቶች | ድርጅታዊ መዋቅር 

ከየት ወዴት

አማራ መንገድ ስራዎች ድርጅት (አመሥድ) በመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ የተሰማራ ደረጃ አንድ ተቋራጭ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የተመዘገበ ካለው እድገትና ከህብረተሰቡ ፍላጎት ጋር እኩል የሚራመድ የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታን ተደራሽ ለማድረግ ሲባል በደንብ ቁጥር 71/2002 ዓ.ም በክልሉ መንግስት የተቋቋመ የልማት ድርጅት ነው፡፡  


አመሥድ እስከ 2004 ዓ.ም በአብክመ ገጠር መንገዶች ባለስልጣን ስር ሆኖ በባለስልጣኑ የሙያ፣ የሰው ሀይል እና የግብዓት ድጋፍ ሲደረግለት የቆየና በ2005 ዓ.ም የደረጃ አንድ ተቋራጭነት (GC-1) ህጋዊነት ፈቃድ አግኝቶ ራሱን በመቻል ተቋማዊ አደረጃጀት ፈጥሮ መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ደረጃጀቱንና አሰራሩን በማሻሻል እና ግብዓቱን በማሳደግ በርካታ የመንገድና የሲቪል ስራዎችን በጥራት አጠናቆ ለአሰሪዎቹ አስረክቧል፡፡ በዚህም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋግጥና ደንበኞችን ለማርካት ያስቻሉ ስኬቶች አግኝቷል፤ አሁንም አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

አመሥድ የተቋቋመው የኮንስትራክሽን ገብያውን በማረጋጋት የህብረተሰቡን የመንገድ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም ነው፡፡ አሁን በደረስንበት ዘመን ከሰው ልጅ የደም ስር ጋር እየተነጻጸረ ያለውን የመንገድ ዝርጋታ ስራ እየተመዘገበ ካለው ማህበራዊና ኢኮኖሚ ዕድገት ጋር አጣጥሞ ለማዝለቅ የሃገር በቀል ኮንስትራክሽን ድርጅቶችን ማበረታትና አቅም ማጎልበት ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑ ታምኖበት በስፋት እየተሰራ ይገኛል፡፡ 

በመሆኑም ድርጅቱ የግሉ ባለ ሃብት አሁን ባለው ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊገነባቸው የማይችላቸውን ነገር ግን በጣም አስፈላጊ መዳረሻ መንገዶችን በመስራት ረገድ ያለውን የኮንስትራክሽን ገበያ ክፍተት በመሙላት ህዝቡን የልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የተቋቋመ ድርጅት መሆኑን አምኖ የሚሰራ ድርጅት ነው - አመሥድ፡፡

አመሥድ በማንኛውም የስራ ከባቢ ውስጥ የክልሉን ህዝብ እያገለገለ ያለ ድርጅት ነው፡፡ በየትኛውም የክልሉ ወጣ ገባና እጅግ ሞቃታማ እንዲሁም መሰረታዊ ግብዓቶች ባልተሟሉባቸው ስፍራዎች ሁሉ በይቻላል መንፈስ በመግባትና ሰርቶ በማጠናቀቅ ለአሰሪው አካል እያስረከበ ይገኛል፡፡ ይህም ህዝባዊ ድርጅትነቱን እያሳየ ያለ ድርጅት ያደርገዋል፡፡ በሌላ በኩል አገር አቀፍ ገበያውንም ተቀላቅሎ በሌሎች ክልሎች የአስፓልት መንገድ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ 

ተቋማችን መንገድ የሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮች እናት ነው የሚለውን መርህ በመያዝ የመንግስትን አቋምና የህዝብን ፍላጎት መሰረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡ ያለ መንገድ ተደራሽ የምናደርገው ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ልማት ባለመኖሩ የመንገድን መሰረተ ልማት ከማንኛውም የልማት ዘርፍ ነጥሎ ማየት አይቻልም፡፡ ድርጅታችንም  ይህንን ተገንዝቦ እየፈጸመ ይገኛል፡፡ ከዚህ ባሻገር ሰንቆ የተነሳውን በክልሉና በሃገሪቱ ብሎም በመምስራቅ አፍሪካ በመንገድ፣ በድልድይ እና በሌሎች የስቪል ወርክ ሥራዎች ግንባታ ዘርፍ ተወዳዳሪና ተመራጭ ሆኖ የማየት ራዕዩን ለማሳካት በጥሩ መሰረት ላይ ይገኛል፡፡ 

ድርጅቱ በአሁኑ ሰዓት ለዘርፉ የሚያስፈልጉ ሁሉም አይነት የስራ መሳሪያዎች በበቂ መጠንና ጥራት ያሉት ሲሆን በሰው ሀይል ረገድም ተልዕከኳቸውን ሊወጡ የሚችሉ ቋሚ እና ኮንትራት ሰራተኞች አሉት፡፡ከዚህም በላይ ድርጅቱ በየአመቱበሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች ከ2ሽ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ጊዜያዊ የስራእድል እየፈጠረ ይገኛል ፡፡ አደረጃጀቱ በዋና መስሪያ ቤት ደረጃ ዋና ስራ አስኪያጅ ፣ በ3 ምክትል ስራ አስኪያጅ እና በነዚሁ በሚመሩ 3 ዋና እና 6 ደጋፊ የስራ ሒደቶች የተዋቀረ ሲሆን፡፡ ድርጅቱ በአሁኑ ሰዓት ከ10 በላይ ዋና ዋና ፕሮጀክቶች ይዞ እየፈጸመ ይገኛል፡፡

ራዕይ

በክልሉና በሃገሪቱ ብሎም በምስራቅ አፍሪካ በመንገድ፣በድልድይ እና በሌሎች የሲቪል ሥራዎች ግንባታ ዘርፍ ተወዳዳሪና
ተመራጭ ሆኖ ማየት፤

ተልዕኮ

በአማራ ክልልና በሀገሪቱ ውስጥ በሚካሄዱ መንገዶችና ድልድዮች ግንባታ፣ደረጃ ማሻሻልና ጥገና እንዲሁም በሌሎች ስቪል ሥራዎች ቀጣይነት ያለው ተሣትፎ በማድረግና ተወዳዳሪ በመሆን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አዋጭነት ያላቸውን መንገዶችና ድልድዮች የአካባቢ ደህንነትን ባገናዘበ ሁኔታ በመገንባት የመንገድ አውታሮችን ከማስፋፋትና ከማሻሻል ባሻገር ለክልሉ ተደማሪ መዋለንዋይ ማፍራት ነው፤  

ዋና እሴቶች

  • ተልዕኳችንና ርዕያችንን ለማሣካት በቁርጠኝነት እንስራለን፤
  • በውጤት መለካትን እናምናለን፤
  • የሥራ ባህልን በወጣቱና በሰራተኛው ዘንድ እናሰርፃለን፤
  • የውጤታችን መለኪያ ፈርጅ ብዙ እናደርጋለን፤
  • ትርፋማና ወጪ ቆጣቢ የአሰራር መርህን እንከተላለን፤
  • የኪራይ ሰብሣቢነት አስተሣሰብን አጥብቀን እንታገላለን፤
  • ለወጣቶችና ለሴቶች የሥራ ዕድል መፍጠር የሥራችን አንዱ አካል እናደርጋለን፤
  • ለስነ-ምግባር መርሆዎች እንገዛለን፤

አገልግሎቶች

  • መንገዶችንና ድልድዮችን መገንባት፣ ደረጃ ማሻሻልና መጠገን፤
  • ሌሎች የሲቪል ሥራዎችን ማከናወን፤
  • የኮንስትራክሽን ገበያውን ማረጋጋት፤
  • የግንባታ መሣሪያዎችንና ቁሣቁሶችን ማምረት፣ማስመጣት፣ማከራየትና መሸጥ፤
  • በልማቱ ውስጥ ብቁ ተዋናይና ውጤታማ መሆን፤
  • የአሰራር እና የውጤት ሞዴል መሆን እና፤
  • በኢንቨስትመንትና በአክሲዮን ገበያው መሣተፍ፤

ድርጅታዊ መዋቅር

Organogram