የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች 69.8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን የደንበጫ ፈረስ ቤት ሰቀላ አስፓልት መንገድ ሥራ ፕሮጀክት የሥራ እንቅስቃሴ ጎበኙ፡፡

feres bet
የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች 69.8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን የደንበጫ ፈረስ ቤት ሰቀላ አስፓልት መንገድ ሥራ ፕሮጀክት የሥራ እንቅስቃሴ ጎበኙ፡፡

በጉብኝቱ የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አስማማው ዓለማየሁን ጨምሮ ሌሎች የኮር አመራር አባላት ተገኝተው እስካሁን በፕሮጀክቱ የተከናወኑ ተግባራትን ከጎበኙ በኌላ የፕሮጀክቱን አፈጻጸም አሁን ካለበት በተሻለ ለማስቀጠል የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከፕሮጀክቱ ሰራተኞች ጋር ገምቢ ውይይት አካሂደዋል።
የፕሮጀክት ሃላፊ አቶ ብሩክ በሪሁን እንደገለጹት በፕሮጀክቱ እስካሁን ባለው አፈጻጸም
 218,450 ሜ3 የመሬት ቆረጣ፣
 1384 ሜ3 የሙሊት ሥራ፣
 8.2 ኪ.ሜ የተለዋጭ መንገድ ግንባታ፣
 86 ሄክታር የአፈር ጠረጋ ስራ፣
 4938 ሜ3 የመንገድ ድልዳሎ ስራ፣
 290,000 ሜ3 የሴሌክት ማቴሪያል ክምችት፣
 11,000 ሜ3 የጠጠር ክምችት እንዲሁም
 ለአማካሪና ለድርጅቱ ሰራተኞች የካንፕ ግንባታ ሥራ በአማካይ 90% ማከናወን ተችሏል።
በጉብኘቱ ወቅት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አስማማው ዓለማየሁ የደንበጫ ፈረስ ቤት ሰቀላ አስፓልት መንገድ ሥራ ፕሮጀክት ቀድሞ ከነበረው የተፋዘዘ የሥራ እንቅስቃሴ ወጥቶ በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በውይይት መድረኩም የፕሮጀክቱ ሃላፊ እና ሰራተኞች ፕሮጀክቱን በታቀደለት ጊዜ ገንብቶ ለማጠናቀቅ እንቅፋት ይሆናሉ ባሏቸውና ከፕሮጀክቱ አቅም በላይ የሆኑ ችግሮችን ማለትም ያለቀለት ዲዛይን አለመቅረብና መንገዱ የሚገነባበት ክፍል ከሶስተኛ ወገን ጽዱ ያለመሆን ችግሮች በፕሮጀክቱ ባለቤት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በኩል በአስቸኳይ እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል። በተጨማሪም በመንገድ ግንባታው ወቅት ለስራ የማይፈለግ የተቆረጠ አፈር ማስወገጃ ስፍራ እጦት ከወረዳ አስተዳደሩ ጋር በመነጋገር እንዲፈታላቸው እንዲሁም በዋና ቢሮ በኩል መቅረብ ያለባቸው ዋና ዋና ግብዓቶች ጥያቄ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጣቸው አሳስበዋል።
የፕሮጀክቱ ሰራተኞች አክለውም ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ ከቀጠለ እና የግብዓት መዘግየት ችግር ከተፈታ የፕሮጀክቱን አፈጻጸም አሁን ካለበት በተሻለ ደረጃ ከፍ ማድረግ እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በመጨረሻም የድርጅቱ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች የፕሮጀክት ማኔጅመንቱ ለፕሮጀክቱ የሥራ አፈጻጸም ተግዳሮት ናቸው ብሎ ያስቀመጣቸውን ዋና ዋና ጉዳዮችን ሁሉም የሥራ ዘርፎች አቅም በፈቀደ መጠን እግር በእግር እየፈቱ በመሄድ እና ፕሮጀክቱን በልዩ ሁኔታ የመከታተል እና የመደገፍ ሥራ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥላል። በተጨማሪም ፕሮጀክቱ በቀረበለት ግብዓት ልክ ወጭ ቆጣቢ በሆነ መንገድ መስራት እና የተሰሩ ስራዎችን ፈጥኖ ወደ ገንዘብ የመቀየር ተግባርን ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ አቅጣጫ ተቀምጧል።