ክቡር ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት በባህር ዳር ከተማ እየተገነባ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ጎበኙ።

photo of Mr. Arega
ክቡር ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት በባህር ዳር ከተማ እየተገነባ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ጎበኙ።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ አረጋ ከበደ አማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት በባህር ዳር ከተማ እየገነባው በሚገኘው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ምሽት ላይ ተገኝተው ተዘዋውረው በመመልከት ሰራተኞችን አበረታተዋል። በጉብኝቱ ከርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አህመዲን ሙሀመድ፣ የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማውን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ እና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ተሳትፈዋል።

በጉብኝቱ ወቅት አስተያየታቸውን የሰጡት ክቡር ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በባህር ዳር ከተማ እየተገነባ ያለው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ምሽትን ጨምሮ በሦስት ፈረቃ እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰው በሌሊቱ ፈረቃ የሚሠሩ ሠራተኞችን ለማበረታታት ጉብኝት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። በክልሉ ከባህር ዳር በተጨማሪ በሁሉም ሪጅኦፖሊታንት ከተሞች የኮሪደር ልማቱ እንዲሠራ አቅደን እየተንቀሳቀስን ሲሉ አመላክተዋል።

በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማና መሠረተ- ልማት ቢሮ ኀላፊ ዶ/ር አህመዲን ሙሀመድ በበኩላቸው ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ ሰውን ተኮር የኮሪደር ልማት መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው በባህር ዳር ከተማ በአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት እየተገነባ የሚገኘው ልማት የኅብረተሰቡን ጥያቄ ለመፍታት የሚያስችል እና የከተማዋን የረጅም ጊዜ የእድገት ህልም ታሳቢ ያደረገ ሥራ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ሌላው በጉብኝቱ ወቅት አስተያየታቸውን የሰጡት የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት የሚገነባው የኮሪደር ልማትን በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ተቋራጩ ከቀኑ በተጨማሪ በምሽትም ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸው ፕሮጀክቱ ከሥራ ዕድል ፈጠራ እና ከእውቀት ሽግግር አኳያም ጠቀሜታው ጉልህ መሆኑን ገልጸዋል።

በአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት የኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ገበያው መንግስቴ በበኩላቸው አማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ከሌሎች ፕሮጀክቶች ያገኘውን ልምድ በመጠቀም ይህን ፕሮጀክት ጥራቱን አስጠብቆ በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየሰራ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።