አማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት በርካታ የመንገድና ህንጻ ግንባታዎችን ገንብቶ አጠናቋል፤ እየገነባም ይገኛል፡፡ ድርጅቱ ከገነባቸው እና እየገነባቸው ከሚገኙ ፕሮጀክቶች መካከል የአብዛኛዎቹን የማማከር ስራ የሰራው ደግሞ የአብክመ መንገድና ህንጻ ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ሥራዎች ድርጅት ነው፡፡ እኛም የአብክመ መንገድና ህንጻ ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ሥራዎች ድርጅት የማማከር ስራ በሰራባቸው የግንባታ ፕሮጀክቶች አማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ያሳየውን የመፈጸም አቅም እንዴት ያዩታል ስንል ዋና ስራ አስኪያጁን አቶ ጥላየ ቢተውን ጠይቀናቸዋል፡፡
የአብክመ መንገድና ህንጻ ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ሥራዎች ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥላየ ቢተው እንደገለጹት ድርጅታቸው አማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ከገነባቸው ፕሮጀክቶች መካከል ከ10 በላይ የህንጻ እና ከ10 በላይ የሚሆኑ የመንገድ ፕሮጀክቶችን የማማከር ስራ ሰርቷል፡፡ አማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት እነዚህን የግንባታ ፕሮጀክቶች በሚፈለገው ጥራት ገንብቶ በማጠናቀቅ ያስረከበ ሲሆን አሁንም እየገነባቸው ያሉ ፕሮጀክቶች አሉ ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ ድርጅቱም የመፈጸም አቅሙን ከጊዜ ጊዜ እያሳደገና ከክልሉ አልፎ የፌዴራል መንግስት ፕሮጀክቶችን እየገነባ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም አሁን ባለው አፈጻጸም አማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር ተስፋ የሚጣልበት ድርጅት ሆኗል ብለዋል፡፡ ዋና ስራ አስኪያጁ አክለውም ድርጅቱ አሁን ያለውን ጥንካሬ ካስቀጠለና የመፈጸም አቅሙን ይበልጥ ለማሳደግ ጥረት ካደረገ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያስቀመጠውን ርዕይ ማሳካት እንደሚችል አስረድተዋል፡፡