የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ከደጋ ዳሞት ወረዳ አስተዳደር ጋር የትውውቅ መድረክ አካሄደ።

ዳሞት

የደንበጫ የፈረስ ቤት 69.8 ኪሎ ሜትር አስፓልት ኮንክሬት መንገድ ስራ ለመገንባት ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ጋር ሃምሌ 3/2012 ዓ.ም ውል የተፈራረመው አማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ከደጋ ዳሞት ወረዳ አስተዳደር የጋራ የትውውቅ እና የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡
የጋራ የውይይት መድረኩን የደጋ ዳሞት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዋለ እንዳለ እና የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አስማማው ዓለማየሁ በጋራ በመሆን በዳቦ ቆረሳ ስነ ስርዓት አስጀምረዋል፡፡
በውይይት መድርኩ የደጋ ዳሞት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዋለ እንዳለ፣ የወረዳው አመራሮች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ሴቶች እና ወጣቶች የተገኙ ሲሆን ከአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አስማማው ዓለማየሁን ጨምሮ የድርጅቱ ኮር አመራሮች እና የማኔጅመንት አባላት ተገኝተዋል፡፡
የደጋ ዳሞት ወረዳ አስተዳዳሪ ለመድረኩ ተሳታፊዎች ድርጅቱ የሚገነባውን አስፓልት ኮንክሬት መንገድ ስራ ለማስጀመር የሚያግዙ ሃሳቦችን አስመልክቶ አጭር የውይይት መነሻ በማቅረብ ከአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አስማማው ዓለማየሁ ጋር በመሆን ውይይቱን በጋራ አካሂደዋል፡፡
የቀረበውን የመነሻ ሃሳብ መሰረት በማድረግ አቶ ትዕዛዙ ስንሻው እና አቶ አለሙ ዘለቀ የወረዳው ማህበረሰብ ደረጃውን የጠበቀ መንገድ ያልነበረው በመሆኑ ምክንያት ለበርካታ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ሲዳረጉ መኖራቸውን በብሶት አንስተዋል፡፡ በሌላ በኩል የመንገዱ ደረጃ፣ በዋና ከተማ ውስጥ እና በንኡስ ከተሞች ላይ የሚያለፈው የአስፓልት መንገዱ ስፋት እና መንገዱ መቸና የት ይጀመራል የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተዋል፡፡
በተጨማሪም ተሳታፊዎቹም ድርጅቱ በክልሉ መንግስት የተቋቋመ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ የሆነ የመገንባት አቅም እንዳለው ተናግረው የደንበጫ ፈረስ ቤትን አስፓልት ኮንክሪት መንገድ በተቀመጠለት ጊዜ በጥራት ገንብቶ በማጠናቀቅ ከነጭ አምላኪነት አውጥቶ የራሳችንን ችግር በራሳችን የመፍታት አቅም እንዳለን የምናይበት እንደሆነ ተስፋ አለን በማለት ሃሳባቸውን በመድረኩ አቅርበዋል፡፡
ከመድረኩ ለተነሱ ጥያቄዎች የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ግርማው በለጠ የመንገድ ግንባታ ባለቤቱ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አማካሪ ቀጥሮ ለማስጀመር የሚያስችሉ ሁኔታዎች ሲጠናቀቁ በኩንትራቱ መሰረት የሚጀመር ይሆናል፡፡ መንገዱ በዋና ከተማው ፈረስ ቤት ባለሁለት አካፋይ ሁኖ 29.5 ሜትር ስፋት እና የ6.7 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን በንኡስ ከተሞች ደረጃ 12 ሜትር ስፋት ይኖረዋል፡፡ በአጠቃላይ መንገዱ ደረጃውን የጠበቀ አስፓል ኮንክሪት እንደሆነ ለመድረኩ ተሳታፊዎች ገልፀዋል።
በመጨረሻም የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አስማማው ዓለማየሁ ለውይይቱ ተሳታፊዎች የደንበጫ ፈረስ ቤት የ69.8 ኪሎ ሜትር አስፓልት ኮንክሬት መንገድ ሥራ ፕሮጀክትን በተቀመጠለት ጊዜ በጥራት ገንብቶ ለማጠናቀቅ ድርጅቱ ተግቶ እደሚሰራ በአማራ መንገድ ሥራዎች አመራር እና ሰራተኞች ስም ቃል በመግባት የኳሪ ሳይት፣ የሴሌክት ማቴሪያል እና የሰራተኞች መኖሪያ ካምፕ ቦታ ልየታና መረጣ ተካሂዶ መድረኩ ተጠናቋል።