‹‹ኅብር ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ክልላችን የሚኮራበት ተቋም ነው››፡፡ አቶ ኃይሌ አበበ የአብክመ ማዕድን ኃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ እና የኮርፖሬሽኑ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ

photo of Mr. Haylie
ኅብር ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ክልላችን የሚኮራበት ተቋም ነው ሲሉ የአብክመ ማዕድን ኃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ እና የኮርፖሬሽኑ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኃይሌ አበበ ገለጹ፡፡ አቶ ኃይሌ ይህንን ያሉት የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የማኔጅመንት አባላት እና የዋና ቢሮ ሰራተኞች በተገኙበት የኮርፖሬሽኑ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡
የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢው እንደገለጹት ኅብር ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በበርካታ ፈተናዎች እያለፈ በሚገኝበት ወቅት ያሉ ፈተናዎችን ሁሉ ተቋቁሞ በታሪኩ ከፍተኛ የሆነውን ትርፍ ማስመዝገብ መቻሉ የሚደነቅ ነው፡፡ ነገን እንገነባለን! በሚለው መሪ ቃሉ የሚታወቀው ኮርፖሬሽኑ የሚገነባቸው መሰረተ ልማቶች ጥራታቸውን የጠበቁና ዘመን ተሻጋሪ ናቸው ሲሉ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢው አስታውቀዋል፡፡

የአመራሩ እርስ በርስ መናበብ ነጋራ አመራር በማረጋገጥ እና የትኩረት ማዕከልን ለይቶ መንቀሳቀስ መቻል ከሰራተኛው የስራ ባህልና የባለቤትነት ስሜት ማደግ ጋር ተዳምሮ ፕሮጀክቶችን ከተያዘላቸው ጊዜ ቀድሞ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ኮርፖሬሽኑ በተግባር አረጋግጧል ያሉት አቶ ኃይሌ አበበ ተቋሙ ያስለማው የተቀናጀ የኃብት አስተዳደር ስርዓት /ERP/ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ በመስራት አሰራርን ለማዘመንና ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የሥራ አመራር ቦርድ አባሏ ወ/ሮ ብርቱካን ሲሳይ በበኩላቸው ኅብር ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን እንደ ቢዝነስ ተቋም የሚመዘነው ትርፉን ከማሳደግ አንጻር ቢሆንም በበርካታ መመዘኛዎች በክልሉ ከሚገኙ የልማት ድርጅቶች የተሻለ አፈጻጸም ያለው ነው በማለት ገልጸዋል፡፡
ወ/ሮ ብርቱካን ሲሳይ አያይዘውም ኮርፖሬሽኑ ራሱን ከአቻ ተቋማት ጋር ሲያወዳድር የዕይታ አድማሱን በማስፋት ከክልሉ ወጣ ብሎ ከሌሎች ሀገር አቀፍና አለምአቀፍ ኮንትራክተሮች ጋር መሆን ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም በ2018 በጀት ዓመት ካለፈው በጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ አልሞ መስራት እንደሚገባ ያነሱት የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢው አቶ ኃይሌ አበበ ይህን አፈጻጸም ማስቀጠል ከተቻለ ኮርፖሬሽኑ በ2030 በአፍሪካ ተመራጭ የኮንስትራክሽን ተቋራጭ ለመሆን ያስቀመጠውን ራዕይ ማሳካት እንደሚችል አረጋግጠዋል፡፡
workers